
የውይይት መድረኩን የመሩት የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የኘላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በቀረበው የ2017 ዓ.ም አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2018 ዓ.ም ዕቅድ ዙሪያ ማብራሪያ በሚያስፈልጋቸው ነጥቦች ላይ የቦርዱ አባላት ሀሳብ እንዲሰጡበት አድርገዋል።
የቦርዱ አባላትም በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው የጀመራቸውን የሪፎርም ስራዎች አጠናክሮ እና ቅድሚያ ሰጥቶ ሊቀጥልበት እንደሚገባ በአፅንኦት አሳስበዋል።
የስራ አመራር ቦርዱ ሰብሳቢ የኘላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም (ዶ/ር) በበኩላቸው የቦርድ አባላት የሰጡትን አስተያየት እንደሚጋሩ ገልፀው ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ ምርምር ብሎም ማህበረሰብ አገልግሎት ያሳያቸውን እምርታዎች በ2018 የትምህርት ዘመንም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። በቦርዱ በኩልም አስፈላጊው እገዛ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለፁት።
በውይይቱ ላይም የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ተገኝተዋል። መከላከያ ሰራዊቱን በምርምር እና በትምህርት ለማሳደግ እየተደረገ ያለውን ስራ ዩኒቨርሲቲውን በተገቢው አግባብ በመደገፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ኘሬዝዳንት ብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ በ2017 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲው በሁሉም መስኮች ላስመዘገባቸው ውጤቶች የስራ አመራር ቦርዱን ጨምሮ የመከላከያ ሚኒስቴር ያደረገው ድጋፍ ላቅ ያለ መሆኑን ጠቅሰው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ኘሬዝዳንቱ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው የጀመራቸው የሪፎርም ስራዎች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶባቸው የሚከናወኑ መሆኑንም ገልፀዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ እንዲሁም የስራ አመራር ቦርዱ አባላት በዩኒቨርሲቲው በቀጣዩ የ2018 የትምህርት ዘመን በሁለተኛ እና በመደበኛ ድግሪ ትምህርታቸውን ለመከታተል የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎችን አበረታተዋል።
ለ2018 የትምህርት ዘመን ቅድመ ዝግጅት በጊቢው እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም ተዟዙረው ተመልክተዋል።